About us

ስያሜ

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት (ዓትኢመ)

መግቢያ

በተከታታይ በሊቢያ ፤ ሌባኖን ፤ ሳውዲ አረቢያና በኩዌይት በኢትዮጵያዊያን ፤ በተለይ ሴቶች ላይ በጅምላ የደረሰውና የሚደርሰው ኢ-ሰብአዊ ግፍ የዓለም ሕብረተሰብና የተባበሩት መንግሥታት የሰራተኞች ድርጅት የደነገጉትን ሕግና መመሪያ ይጻረራል ፤ በኢ-ሰብአዊነቱና ሕገ-ወጥነቱ ተወዳዳሪ የለውም። ለዚህ በተከታታይ ለተከሰተ ውርደትና ሰቆቃ ከመተባበርና ፤ ተቆርቋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያስተናገድ ጠንካራ የሰብአዊ መብቶች ጠበቃና ተከላካይ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከማቋቋም ሌላ አማራጭ የለም።

በሕዝብ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘችው ኢትዮጵያ፤ ዜጎቿ በሃገራቸው የመሰብሰብ፤ የመናገር፤ የመንቀሳቀስ፤ የግል ሃብት የመያዝ፤ የማምለክ፤ በየትኛውም የሃገራቸው ዳር ድንበር የመኖርና የመስራት፤ በሃገራቸው ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ፤ በፍርድቤት ያለምንም አድልዎና የፖለቲካ ጫና ፍትህ የማግኘት መብታቸውን መነፈጋቸው ዓለም ያወቀው ሀቅ ሆኖ ሳለ ስለነዚህ ሰብአዊ መብቶች መከበር የሚሟገት፤ ጠንካራ፤ ዘላቂነት ያለውና በአንድ ድምፅ የሚናገር ተቋም አለመኖሩ ችግሩን አባብሶታል።

ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ወገኖችም ባሉበት አገርና አካባቢ የመመረጥና የመምረጥ መብታቸውን ተጠቅመው የኢትዮጵዊያን ወገኖቻቸውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ደጀን እንዲሆኑና ድጋፍ እንዲሰጡ የሚያስችል ፤ ለጋስ መንግሥታትና ድርጅቶች የሚሰጡት እርዳታ ከሰሰብአዊ መብቶችና ነጻነት ጋር እንዲያያዝ ጫ ናማድረግ የሚችል ፤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ የሰብአዊ መብት ድርጂቶች ጋር በመቀራረብና በመፈላለግ አብሮ ተባብሮ መስራት የሚችል ፤ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት አጢኖና አጥንቶ መፍትሄ መፈለግ የሚችል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና ጠንካራ የሆነ ተቋም መመስረት ወቅታዊና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አምነንበታል።

ራዕይ

የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት ራዕይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሰብአዊ መብት ተከብሮ ማየት ነው።

ተልእኮ

የድርጅቱ ዋና ተልእኮ የዓለም አቀፍ ሕግና የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር እውቅና በሰጠው መሰረት የኢትዮጵያዊያን ሰብአዊ መብት እንዲከበር ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ በዘላቂነት መስራት ፤ ጥናቶችን ፤ ውይይቶችን ማካሄድ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ መስጠት ናለተጎዱ ካሳ የሚከፈልበትን ዘዴና መንገድ መፈለግ ነው።

ዓላማዎች

የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት ቀጥሎ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ዓላማዎች ይኖሩታል

  • ኢትዮጵያዊያን ለመብታቸው እንዲቆሙና እንዲታገሉ አቅማቸውን ማጠናከር ፤ ማስተማርና ያልተቆጠበ ምክርና የሃሳብ ድጋፍ መስጠት፤
  • በሰብአዊ መብቶች ላይ ፤ ከተመሳሳይ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመተባበር ፤ ጥናቶች ፤ ምርምሮች ፤ ትምኅርታዊ ስብሰባዎችና ውይይቶች ፤ አቤቱታዎችና ክሶች ማካሄድ ፤
  • ለተከታታይ ስደት መጋቢ የሆነውን በኢትዮጵያ ያለውን የሰው ኃይል ንግድ (Human Trafficking) መረብ ተከታትሎ ማጥናት ፤ መመርመር ፤ ከሌሎች የሰብአዊ ድርጂቶች ጋር በመተባበር ማጋለጥ ፤ ይህ ንግድ እንዲቆም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያልተቆጠበ ጭነት ማድረግ፤
  • ኢትዮጵያዊያን በያሉበት የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን ተጠቅመው ለኢትዮጱያዊያን ሰብአዊ መብት አምባሳደር እንዲሆኑ መቀስቀስ
  • የተባበሩት መንግሥታትና የመንግሥት ያልሆኑ ሰብአዊ አገልግሎች ሰጪ ድርጂቶች ሰብአዊ መብታቸው ለተገፈፈ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲሰጡ መቀስቀስ ፤ አብሮ መስራት ፤
  • የአሜሪካ መንግሥት ምክር ቤትና የሌሎች አገሮች ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶችና ነጻነት እንዲከበሩ ጥረት እንዲያደርጉ ከሌሎች ጋር በመደጋገፍ መስራት ፤ ማንኛውም እርዳታ ከሰብአዊ መብቶችና ነጻነት መከበር ጋር በጣምራ እንዲታይ መቀስቀስ ፤ ለዚህ የሚሆኑ የስራ ቡድኖችን ቢያንስ በእንግሊዝ አገር ፤ በአውሮፓ የጋራ ማህበር / ብራሰልስ ፤ በደቡ ብአፍሪካ በካናዳና በአሜርካ ፤ በአውስትራሊያ እንዲቋቋሙ ማድረግ ፤ ሃላፊነቱን በሙሉ ለእነዚህ ሰብስቦች (grassroots support groups) መስጠት፤
  • ድርጅቱ ቀጥታ የሆነ መረጃ እንዲኖረው ፤ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩባቸው አገርች ጥናትና ዘገባ ለማድረግ ብቃትና እውቅና ያለው ልኡካን መሰየምና መላክ ፤ ቡድኑ የተጎዱ ወገኖቻችን በቀጥታ እንዲያነጋግር ማድረግና ዘገባውን ለሕዝብ ማቅረብ፤